የደብረ ታቦር ቀጠና አልማ ጽ/ቤት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 2 የገጠር ወረዳዎችና ለአንድ ከተማ አስተዳደር ከ320 ሺህ ብር በላይ ለልማት

የሚውል የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ 

አማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ የደብረታቦር ቀጠና የዕቅዱን 98% የተገበረው የአንዳቤት ወረዳ በአልማ ለሚተገበር ለማህበራዊ ልማት እንቅስቃሴ ድጋፍ የሚያውለው 175 ሺህ ብር ሲሸለም በተመሳሳይ የዕቅዱን 92.17% በመተግበር በዕለቱ የምስራቅ እስቴ ወረዳ ሁለት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ተበርክቶለታል፡፡ ከከተማ አስተዳደሮች ምድብ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር 91% ዕቅዱን በመፈፀም ላሳየው አበረታች እንቅስቃሴ በተመሳሳይ ለልማት ስራው ማገዣ የሚያውለው 100,000 ብር ተሸልሟል፡፡

 ተሸላሚ የገጠር ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች አመራረጥም የተሻለ የአባል ቁጥር በአዲስ ያፈራና ነባር አባላትን ያስቀጠለ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን አባል ያደረገ፣ በአንፃራዊ የተሻለ ለልማት የሚውል ሀብት ያሰባሰበና በተሰበሰው ገንዘብ የታቀደውን ፕሮጀክት የተገበረ ወይም መተግበር የጀመረ የሚሉትን በዋናነት ማዕከል ያደረገ መሆኑን የደብረታቦር ቀጠና አልማ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳፍንት ልብሴ በሪፖርታቸው አስረድተዋል፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ አያይዘውም ለሽልማት የበቁት ወረዳዎች ምዘና አዲሱን የማህበሩን የBSC አሰራር መሰረት ያደረገ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡

        
ሌሎችም ከየምድባቸው ቀጣይ ደረጃዎችን የያዙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በፍሬም ከታሸጉ ፎቶ ግራፎች እስከ ላፕቶፕ ኮምፒውተር በዕለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ጐንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ እሸቱ ካሴ እጅ የተቀበሉ ሲሆን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ወረዳዎችም የአፈፃፀም ተሞክሯቸውን ለሌሎች አካፍለዋል፡፡

የደቡብ ጐንደር ዞን አመራሮች፣ የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ዋናው ጽ/ቤት ተወካዬች፣ በዞኑ የወረዳ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተካሄደው የሽልማት ስነ-ስርዓት በቀጣይ በ2006 ዓ.ም በዞኑ ለመተግባር የቀረበውን ዕቅድ ከ2005 ዓ.ም አፈፃፀም በበለጠ ለመተግበር የሚያስችል የፉክክር መንፈስ እንደሚፈጥርም ከዕለቱ ይተላለፉ ከነበሩ መልዕክቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡

 


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede