ባለፉት ሁለት አመታት እየተተገበረ ያለው የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮጀክት ከ58 ሽህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ገለጸ፡፡

በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም-2 ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ የሽመቤት አይኔ ለማህበሩ ህዝብ ግንኙነት እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸዉ አራት ዞኖችና አምስት ወረዳዎች ፕሮግራሙ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በውሃና በገጠር መንገድ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ አገልግሎት ሰጭዎችና ተቀባዮች  ይበልጥ ተቀራርበው በጋራ መስራት እንዲችሉ የሚያግዙ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራቱን ገለጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው በምስራቅ ጎጃም- ደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፤ በደቡብ ወሎ- ቃሉ ወረዳ፤ በደቡብ ጎንደር- እብናትና ፎገራ ወረዳዎች እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ  አካባቢዎች የሚገኙት ቁጥራቸዉ ከ58 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች እዳረጋገጡት በተለዩት ዘርፎች የሚቀርቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ያሉ ችግሮችን በተደራጀ መልኩ በመለየት፣ ቅደም ተከተል በመስጠትና የጋራ በማድረግ በራሳቸዉ የሚፈቱትን ይፈታሉ፤ ሌሎችን ደግሞ በአገልግሎት ሰጭው አካል በኩል እንዲፈቱላቸዉ ይጠይቃሉ፤ መፈታታቸውንም ይከታላሉ፡፡

በእነዚሁ አካባቢዎች የሚገኙ አገልግሎት ሰጭዎች በበኩላቸው አገልግሎት ተቀባዩ ማህበረሰብ እንዲፈቱለት የሚያቀርባቸውን ችግሮች በማዳመጥ፤ የጋራ ውይይት በማካሄድ የጋራ የመፍትሄ እቅድ እንደሚያዘጋጁ አስረድተዋል፡፡

በአገልግሎት ሰጭወችና ተቀባዮች መካከል የጋራ መደማመጥና ዉይይት እዳበረ እንደሚገኝ ያብራሩት ወ/ሮ የሽመቤት በጋራ ችግሮችን  የመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ልምድ እዳበረ መምጣቱን ገልጸዉ፤እቅዳቸዉ በአግባቡ ስለመተግበሩና የማህበረሰቡ ችግሮች በተቀመጠላቸዉ አግባብ ስለመፈታታቸዉም የመገምገሚያ ስልት አስቀምጠዉ እየተገበሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እየተተገበረባቸው ባሉ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ሰጭዎች መጠየቅ አለብኝ በሚል ስሜት፤ አገልግሎት ተቀባዮችም እንዲሁ በአገልግሎቶች ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት፣ በመጠየቅ፣ በማህበረሰቡ የሚፈቱትን በመፍታትና በአገልግሎት ሰጭዎች የሚፈቱትን ተከታታይ ክትትል በማድረግ የድርሻየን አበረክታለሁ ሲሉ ከመደመጥ አልፈው መተግበር መቻላቸው የፕሮጀክቱ ለውጥ ማሳያዎች ናቸውም ተብሏል፡፡

እንዳለው  የሻምበል

ከአልማ    


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede