አልማ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ

አማራ አቀፍ ልማት ማህበር/አልማ/ በ60 ሚሊዮን ብር ወጭ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ፕሮጀክት ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በልማት ማህበሩ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ አበረ መኩሪያዉ የህጻናት የንባብ ባህልና ክህሎት ለማሻሻል በክልሉ ት/ ቢሮ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት አልማ ለህጻናት የንባብ ባህልና ክህሎት መሻሻል ከዚህ ቀደም ያከናወናቸዉንና የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ጠቅሰዉ  በአጋር አካላትና በዘርፉ የተገኙ ግብዓቶችን በማጠናከር በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡ ፡                                                                                  

በክልሉ 3 ዞኖችና 21 ወረዳዎች በሚገኙ 315 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የሚማሩ ህጻናትን የንባብ ባህልና ክህሎት ለማሳደግ በዚሁ በሚተገብረዉ  ፕሮጀክት የህጻናትን የንባብ ጥግ ማዘጋጀት፣ለመምህራን ስልጠናዎችን መስጠት፣ የወላጅ-መምህር-ተማሪ የኮሚቴዎችን ማቋቋምና በስልጠና ማገዝ እንዲሁም አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን ማሟላትና ማቅረብን እንደሚያካትትም ከምክክር መድረኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የንባብ ባህልና ክህሎትን በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች በማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያለመዉ ፕሮጀክቱ በቀጣይ አራት አመታት በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር/አልማ/ የሚተገበረዉ ከዩ ኤስ ኤይድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና ከአሜሪካ ሕጻናት አድን ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑንም በምክክር መድረኩ ተገልጿል፡፡

አልማ ቀደም ሲል ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሰሜን ጎነደር ፤ በኦሮሞና በዋግኸምራ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በሚገኙ 6 ወረዳዎችና 42 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ  የህጻናትን የንባብ ባህልና ክህሎት ለማሳደግ የተገበረዉ ፕሮጀክት በምክክር መድረኩ ለቀረቡት ተሞክሮዎች ዋና ግብዓት መሆኑም ተመልክቷል ፡፡

 


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede