አልማ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ  ያስገነባቸው የትምህርትና ጤና ተቋማት ተመርቀው

አማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ / በሰሜን ጐንደር ዞን ጐንደር ዙሪያ ወረዳ 10 ቀበሌዎች ኤ ግሊመር ኦፍ  ሆፕ  ከተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት በተገኘ  ድጋፍ እንዲሁም በወረዳው አስተዳደርና በአካባቢው  ህብረተሰብ የጋራ ትብብር ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ  ያስገነባቸው የትምህርትና ጤና ተቋማት ተመርቀው አገልገሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

የተቋማት ምረቃ        

ከተመረቁ ት/ቤቶች መካከል

መጋቢት 4 /2008 ዓ.ም. የተመረቁት እነዚሁ ተቋማት በሠባት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተገነቡ የውስጥ ቁሳቁስ የተሟላላቸው አርባ  የመማሪያ ክፍሎች ያላቸው  አስር ብሎኮች፤ የአንድ ጤና ጣቢያ  የህክምና አገልግሎት መስጫ /IPD/ እና አንድ ጤና ኬላ ያካተቱ ናቸው ፡፡

ለምባ ጤና ጣቢያ        

ለምባ አርባይቱ ጤና ኬላ

በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ /፤ በኤ ግሊመር ኦፍ ሆፕ እንዲሁም በወረዳው አስተዳደርና በአካባቢው ነዋሪዎች ትብብር ተገንብተው የተመረቁት የጤና ተቋማት ከ26 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሠጡ ሲሆን የትምህርት ተቋማቱ ደግሞ  ከ 5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ዋና ስራ አስፈፃሚ  ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠና በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ ሁሉንም የልማቱ ተሳታፊዎች በማመስገን እንደተናገሩት በወረዳው እየተተገበረ ያለው  የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር አፈፃፀም አበረታች መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የ2ኛው ዙርም በበለጠ በተሳካ ሁኔታ እንደሚተገበር ሙሉ እምነታቸውን ገልጸዋል ፡፡

የጐንደር ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው  አልማና ሌሎች የልማት ድርጅቶች ከኤ ግሊመር ኦፍ ሆፕ ፤ ከወረዳዉ መስተዳድርና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት  እየተገበሩት ያለው ልማት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው አመስግነዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤግሊመር ኦፍ ሆፕ ዳይሬክተር አቶ ገብረህይወት አበበ እንዲሁ በተቋማቱ ምረቃ ላይ እንዳስገነዘቡት ማህበረሰቡና የወረዳው መንግስት የተመረቁ ተቋማትን በእንክብካቤ መያዙ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሠጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘዉም በ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ዓመት የሚቆየዉ የተቀናጀ የማህረሰብ ልማት ፕሮጀክት እንደ ጅምሩ ሁሉ ሁላችንም በጋራ በመነቀሳቀስ ከምንጊዜዉም የበለጠ ዉጤታማ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede