አማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/  ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ተማሪዎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማንበብና መፃፍ ክህሎት የሚያሻሽል ፕሮጀክት እየተገበረ ነው፡፡

 በፈረንጆች አቆጣጠር ከጃንዋሪ  15/201 –2018  በክልሉ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ሰሜን ወሎ ዞኖች  በሚገኙ 28 ወረዳዎችና 728 ት/ቤቶች  እየተተገበረ የሚገኘው  የማንበብና መፃፍ ክህሎት ማሳደግ ፕሮጀክት  ከዩ ኤስ አይዲ  በተገኘ 90 ሚሊዮን ብርና  ሴቭ ዘ ችልድረን ኢንተርናሽናል የቴክኒክ ድጋፍ  ይደረግለታል፡፡

 ፕሮጀክቱ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ  ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል   ተማሪዎች ራሳቸውን ችለው ለመማር እንዲነሳሱና   ማንበብ እንዲያዘወትሩ የጎላ አስተዋፅኦ የሚያደርግ  ሲሆን  ፤  በትምህርት ቤቶች ዘንድ ውጤታማ  የመማር ማስተማር ሄደት እንዲካሄድ እያደረገ መሆኑ ተገልጧል፡፡

የንባብና መፃፍ ክህሎት ማሻሻያ ፕሮጀክቱ ተማሪዎችን የንግግር ድምፅ ግንዛቤ ፤የድምፅና ፌደል ግንኙነት አቀላጥፎ ማንበብ፤ የቃላት ዕውቀትና አንብቦ የመረዳት ችሎታቸውን የማሳደግ ግብ እንዳለው ተመልክቷል፡፡

በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ የፕሮግራም ማናጅመንት ም/ዳይሬክተር አቶ መዝገበ አንዷለም እንደገለፁት ልማት ማህበሩ ከአጋር ድርጅቶች ያገኘውን ሀብት ለዚሁ ፕሮጀክት የመደበበት ምክንያት  የክልሉ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማንበብና መፃፍ ክህሎታቸውን በማሻሻል የአዳዲስ መረጃዎች፤ ሀሳቦችና ልምዶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካለው ፍላጎት የተነሳ ነው ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ማንበብና መፃፍ ክህሎት ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት መምህራንና ትምህርት ተቋማት ብቻቸውን ሊወጡት እንደማይችሉ የገለፁት አቶ መዝገበ የተማሪ ወላጆችና ማህበረሰቡ ተቀራርበው ልጆችን ሊያበረታቱና ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ሀላፌ አቶ ተፈራ ፈይሳ በበኩላቸው የህፃናትን የማንበብና መፃፍ ክህሎት ማሳደግ ፕሮጀክት መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለፕሮጀክቱ መሳካት ቢሮው ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን የሚያስፈፅሙ ቁጥራቸው 300 የሚደርሱ   ፤ለአሰልጣኝ አሰልጣኖች ፤የወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ኤክስፐርቶችና ስልጠና በደብረታቦርና ዳንግላ ከተሞች  ተዘጋጅቶ እየተሰጠ መሆኑን አቶ ተፈራ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

አልማ በቀበሌ ደረጃ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች  አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡  

 በቀበሌ ደረጃ ታቅደው የሚተገበሩ  የግንባታ ፕሮጀክቶች  ግልፅና ወጭ ቆጣቢ ከመሆናቸው ባሻገር  በህብረተሰቡ ዘንድ የልማታዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ከፍተኛ ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ  የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ አስታወቀ፡፡

የልማት ማህበሩ በደብረታቦር ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሓለፌ አቶ መሳፍንት ልብሴ  እንደገለፁት በ2008 በጀት አመት በደራ ፤በፎገራ ፤በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ፤ በላይ ጋይንትና ፋርጣ  ወረዳዎች ከአባላት በተገኘ ሀብት   በቀበሌ ደረጃ ታቅደው በህብረተሰቡ የሚተገበሩ   200 የሚደርሱ የጤና ትምህርትና ስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክቶች እየተገበረ ነው፡፡

  እነዚሁ ፕሮጀክቶች በቀበሌ ነዋሪዎች   የፋይናንስ ፤ ጉልበትና ቁሳቁስ አስተዋፅኦ የሚተገበሩ ከመሆናቸውም በላይ  ከዕቅድ ዝግጅት እስከ አፈፃፀም  ድረስ ሙሉ በሙሉ የቀበሌውን  ህብረተሰ በማሳተፋቸው  ግልፅ ፤ ወጭ ቆጣቢና በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ከመጠናቀቃቸው ባሻገር ለኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ዕድል የማይሰጡ ይልቁንም ልማታዊ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን አቶ መሳፍንት አብራርተዋል፡፡

 ልማታዊ ባለሀብቶች አልማን በመደገፍ  የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ   በኩል የሚጫዎቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

  አካባቢን የማልማት እና የነገ ሀገር ተረካቢ የሚሆኑ የተማሩ ወጣቶችን የማፍራት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚጣል ሀላፌነት አለመሆኑ ተገለፀ ፡፡

 በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀሽም ሰይድ  ይህን የገለፁት  በግል ባለሀብት ሙሉ ወጭ የተገነባውን  የአንቻሮ አጠ/1ኛ/ደረጃ ት/ቤት አንድ ብሎክ ባለ 4 የመማሪያ ክፍል መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው ፡፡

በአግማስ ሀላፌነቱ የግል አክሲዎን  ማህበር ባለቤትና የአካባቢው ተወላጅ በሆኑት አቶ ሀጅ ኑሩ አህመድ  ከ2ሚሊዩን ብር በላይ ወጭ ግንባታው የተጠናቀቀው የአንቻሮ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፌያ ግንባታ መንግስት ለጀመረው የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ስራ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት ፤ ዋና አስተዳዳሪው የባለሀብቱ ሙሉ ፈቃደኝነትና ጥረት ለሌሎች ባለሀብቶች አርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

በባለሀብቱ አቶ ሃጅ ኑሩና  በአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ትብብር በወረዳቸው የተገነባው የትምህርት ቤት ማስፋፌያ  ለትምህርት ጥራትም ሆነ የወረዳውን  ልማት በማነቃቃት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 ከልማት ሁሉ የላቀው ልማት የሰውን ልጅ አዕምሮ ማልማት እንደሆነ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ወቅት የገለፁት አቶ ሀጅ ሰይድ ኑሩ  አካባቢያቸውን ለማልማት  ያነሳሳቸው  አማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ በልማታዊ ህብረት ወቅት በፈጠረላቸው ዕድል መሆኑንና  በቀጣይም መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡

 አቶ ሃጅ አያይዘውም የአንቻሮ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቋሚነት መደገፋቸውን እንደማያቋርጡ አስገንዝበው ከዚህ በፊት የተገነቡና ለመማር ማስተማር ሂደቱ አመች ያልሆኑ በእድሜ ብዛት የተጎዱ ሁለት የመማሪያ ብሎኮችን በ1ሚሊዩን ብር ወጭ ለመጠገን ቃል ገብተዋል፡፡

                                                                                                    


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede