አልማ 55 ቢሊዮን ብር ሃብት በማሠባሠብ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታወቀ።
አልማ 55 ቢሊዮን ብር ሃብት በማሠባሠብ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታወቀ። -------------- አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በጋራ በመኾን በተለይ በጦረነት በተጎዱ አካባቢዎች በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ማሻሻያ ዙሪያ ለመሥራት በጎንደር ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱም የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መላኩ ፈንታ፣ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ተስፋየ አያሌው (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትም፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ እና ሌሎች አሥፈጻሚ አካላት ተገኝተዋል። የአማራ ልማት ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ መላኩ ፈንታ አልማ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በጤና እና በትምህርት ዘርፎች በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አንስተዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በ10 ጤና ጣቢያዎች የግንባታ ቁሳቁስ እና የሙያ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። አልማ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ መስጠት ብቻ ሳይኾን የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፍ እንደሚሰጥ ያነሱት አቶ መላኩ በጦርነት ምክንያት ያቋረጡ ተማሪዎች የተፋጠነ ትምህርት እንዲያገኙ ተሠርቷል ብለዋል። ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በጤና ተቋማት ለእናቶች እና ለሕጻናት የተለያየ ግልጋሎት እንዲሰጥ መደረጉንም አንስተዋል። አልማ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በትምህርት፣ በጤና እና በሥራ ዕድል ፈጠራ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል። በቀጣይ አምስት ዓመት ውስጥ አልማ 55 ቢሊዮን ብር ሃብት በመሠብሠብ ማኅበረሰቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠራ በውይይቱ ተጠቁሟል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ አልማ በዞኑ በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል። ዞኑ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዳ መኾኑን አንስተው አልማ እና ዩኒሴፍ በመተባበር በዞኑ ወገራ ወረዳ በጤና እና በትምህርት ዘርፍ ለመሥራት ወደ ትግበራ መግባታቸው የሚያስደስት ነው ብለዋል። የእናቶች እና የሕጻናት ጤና ማሻሻል ፕሮጀክት ወደ ዞኑ መምጣቱ የሚደገፍ መኾኑን ገልጸው ተፈጻሚ እንዲኾኑ የዞኑ አሥተዳደር በቁርጠኝነት ይሠራል ነው ያሉት። የውይይቱ ተሳታፊዎች ፕሮጀክቱ ለእናቶች እና ሕጻናት ጤና መጠበቅ ጉልህ ድርሻ ያለው በመኾኑ ለተፈጻሚነቱ በትኩረት እንሠራለንም ብለዋል።