የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ እውን እንዲሆን ኹሉም ድጋፍ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጥሪ አቀረቡ፡፡

Posted on : May: 23/21
Card image

የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ እውን እንዲሆን ኹሉም ድጋፍ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጥሪ አቀረቡ፡፡

የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ እውን እንዲሆን ኹሉም ድጋፍ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጥሪ አቀረቡ፡፡ ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድነት ፓርክ የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የአማራ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት እንደሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ጭቆና ሲደርስበት እንደነበር አንስተዋል፡፡ ከድህነቱ በላይ በተነዛበት የሐሰት ትርክት የአማራ ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት በየትኛውም ቦታ ተረጋቶ እንዳይኖር ሲደረግ እንደነበረ እና አሁንም ለችግር እየተዳረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ነጥሎ የማስመታት አጀንዳ እንዲዘጋ እና የአጀንዳው ቀጥተኛ ፈጻሚ የሆነውን ኃይል በማስወገድ ሀገራዊ ለውጡ እንዲሳካ የአማራ ሕዝብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ አገኘሁ እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡ እውን እንዲሆን የአማራ ሕዝብ ልጆቹን ገብሯል፤ የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለውጡን ለመቀልበስ የተንቀሳቀሱ የምንግዜም ጠላቶችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የአማራ ሕዝብ፣ ከአብራኩ የወጣው የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አሁን ለመጣው ሰላም የከፈሉትን ዋጋ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ለአማራ ሕዝብ፣ ለአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ሰፊ የመሰረተ ልማት፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን አንስተዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡ ክልሉን ለማልማት እጅ ለእጅ መያያዝ፣ መመካከር፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር አንድ መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ “በኛ ሀገር እጣ ፋንታ ላይ ማንም ሊወስንልን አይችልም፤ በዚህን ሀገር እጣ ፋንታ ላይ መወሰን የሚችሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ናቸው … እጣ ፋንታችንን የምንወስን ከሆነ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን” ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ቅርቃር ውስጥ ለመክተት ጠላቶቿ ከሁሉም አቅጣጫ መነሳታቸውን የጠቀሱት አቶ አገኘሁ “ይህን ጊዜ አሸንፈን እንደምንሻገረው እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በክልሉ ልማት ለማምጣት ያበረከተውን የጎላ አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡ ማኅበሩ የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እና የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት ለአብነት አንስተዋል፡፡ የማኅበሩን ደጋፊዎች፣ አባላትን፣ ባለሀብቶችን ተቋማትን እና ሌሎች አካላትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ ኹሉም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአማራ ባሕል ማእከል ደረጃውን የጠበቀ፣ የገቢ ማስገኛ የሚሆን፣ የአማራ ሕዝቦችን ቱባ ባሕል እና ትውፊት የሚታይበት፣ የማንነታቸው መገለጫ ኾኖ እንዲገነባ ዝግጅት መደረጉን አቶ አገኘሁ ገልጸዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ የባሕል ማእከሉ እውን እንዲሆን መገንቢያ ቦታ በመስጠቱ ረገድ ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን አመስግነዋል፡፡ የባሕል ማእከል ግንባታው እውን እንዲሆን ኹሉም ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ አገኘሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ በዌብሳይት www.amharaweb.com በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Gallary


The News