’ የድል ባለቤት ለመሆን ኢትዮጲያዊነት መንፈስና አንድነት ብቻ በቂ ነው !’’ (ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ በአሜሪካ ዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ)

Posted on : February: 25/22
Card image

’ የድል ባለቤት ለመሆን ኢትዮጲያዊነት መንፈስና አንድነት ብቻ በቂ ነው !’’ (ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ በአሜሪካ ዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ)

አገራችን ከገጠማት ፈተና በአሸናፊነት ለመውጣትና የዘላቂ ድል ባለቤት ለመሆን ኢትዮጲያዊነት መንፈስና ሀገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ሲሉ በኢትዮጲያኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ገለፁ፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ይህን የገለፁት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዋሽንግተን፤ ኦሪገን አይዳሆ እና አካባቢው፤ ሀገረ ስብከት ምዕመናን፤ ካህናትና ዲያቆናት በሳቸውና በሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያ መልዐከ አሚን ዶ/ር ፋሲል አስረስ በኩል የተላከውን 1 ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ብር ወጭ የተደረገበትን 375 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ለደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ርክክብ በተደረገበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ‘’ጀግና ህዝብ በራሱ ወገን ሊጠቃና ሊበደል አይገባም ! አንድነቱን የሚፈታተንና አቅሙን የሚያዳክም ሀሳብና ተግባር መወገድ አለበት ! መጠላለፍና ለጠላት በር መክፈት አያስፈልግም! ‘’ ያሉት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የዘላቂ ድል ባለቤት ለመሆን ከቡድንተኝነት ያለመተማመንና አድሎአዊ ሀሳብና አሰራር በመውጣት ህዝብን በፍትሀዊነት ማገልገል በቂ ነው ! ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላዐከ አሚን ዶ/ር ፋሲል አስረስ በዚሁ ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለፁት ምንም እንኳ ለደቡብ ጎንደር የጦርነት ተጎጅዎች የድጋፍ ዕቅድ አንድ ሚሊየን ወጭ የሚጠይቅ የስንዴ ዱቄት ቢሆንም ፤ ነገር ግን ቦታው ከደረስን በኋላ የወለጋና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች ደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ መኖራቸው በምክትል አስተዳዳሪው መገለፁና የሚኖሩበት ካምፕ ድረስ ሄዶ መጎብኘትና የአምስት መቶ ሽ ብር ተጨማሪ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የደቡብ ጎንደር ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ የእለት ደራሽ ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለፁት በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ምዕመናን፤ ካህናትና ሊቃውንት ወራሪው የትግራይ ሃይል ያደረሰብንን ጉዳት ተመልክተው ለላኩት የዕለት ደራሽ ምግብ በተጠቃሚው ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ብፁዕነታቸውና የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ የድል ባለቤት ለመሆን ኢትዮጲያዊነት መንፈስና አንድነት ብቻ በቂ ነው ! ሲሉ የሰጡን ምክረ-ሀሳብና መፅናናት የዘላለም ስንቅ አድርገን አንመራበታለን ብለዋል ምክትል አስተዳዳሪው ፡፡ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በበኩላቸው በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዋሽንግተን አይዳሆና ኦሪገን አካባቢ ነዋሪዎች ምዕመናን፤ ካህናትና ሊቃውንት ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ላደረጉት የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ በእግዚአብሄር ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ለማበጀት ግን በውጭም በሀገር ውስጥም የምትኖሩ ወገኖች ቀና ትብብርና መተሳሰብ አስፈላጊ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ አማራ ልማት ማህበር በደብረ ታቦር ከተማ እያከናወነ የሚገኘውን የትምህርትና ጤና ተቋማት ተዘዋውረው የጎበኙት ብፁዕ አቡነ ማርቆስና መላዕከ አሚን ዶ/ር ፋሲል አስረስ በቀጣይ ከአማራ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በዘላቂ ልማት ላይ መሳተፍ የሚያስችል ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

Gallary


The News