የአማራ ልማት ማህበር ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለውጤታማ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የክልሉን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል በምንችልበት የተሻለ አጋጣሚ ላይ ነን ሲሉ የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለፁ፡

Posted on : April: 21/22
Card image

የአማራ ልማት ማህበር ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለውጤታማ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የክልሉን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል በምንችልበት የተሻለ አጋጣሚ ላይ ነን ሲሉ የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለፁ፡

ክቡር አቶ መላኩ ፈንታ ይህን የገለፁት የልማት ማህበሩ የቢዝነስ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ በቅርቡ በአምስት አስተዳደር ዞኖች የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ስራቸውን አጠናቆ ግንባታ ለማስጀመር ያዘጋጃቸውን የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች በክልሉ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው ለሚንቀሳቀሱ ከ10 በላይ የመንግስት ልማት ድርጅቶች በባህርዳርነ ባስተዋወቀበት መድረክ ላይ ነው፡፡ አልማ ከልዩ ልዩ አባላትና አጋር ድርጅቶች ከሚያገኘው የልማት ሀብት በተጨማሪ ከፌደራል ሲቪክ ተቋማት ኤጀንሲ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት የራሱን የገቢ ማስገኛ ተቋማት አቋቁሞ እንደ አንድ የልማት ሀብት ምንጭ መጠቀምና ርዕዩን ለማሳካት በመትጋት ላይ መሆኑን የተናገሩት ክቡር አቶ መላኩ ፤ አልማ በደብረ ማርቆስ፤ ፍኖተ-ሰላም፤ ጎንደር ፤ ደብረ ታቦርና ወልድያ ከተሞች ባለ 10 ፎቅ ሁለገብ ህንፃ ፤ የዋንዛየ ፍል ውሀ ሎጅ እና የጢስ አባሊማ የንፁህ መጠጥ ውሀ መፈብረክ ፕሮጀክቶችን የመልካም አፈፃጸም ልምድና አቅም ላላቸው የክልሉ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የልማት ድርጅቶች አወዳድሮ ለመስጠት ወስኗል ብለዋል፡፡ በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የአማራ ውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኮንስትራክሽን ድርጅታቸው የልማት ማህበሩ የፕላትኚዮም አባል ሆኖ በየአመቱ ልማት ማህበሩን የሚደግፍና የክልሉን ህዝብ ህይወት በማሻሻል ረገድ የጋራ ርዕይ እንዳላቸው ጠቅሰው ድርጅታቸው የሚሰጣቸውን የግንባታ ኮንትራት በጥራት ፤ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳና ባልተጋነነ ወጭ ሰርቶ ለማስረከብ ደስተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የመቅዳላ ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ልማት ማህበሩ አሁን የሚገኝበት የዕድገት ደረጃ በዋናነት የክልሉ ህዝብ የጋራ ርብርብና እየተሰጠ የሚገኘው አመራር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው የማህበሩን የግንባታ ፕሮጀክቶች በጥራትና በኮንትራት ውል የጊዜ ገደብ ከማስረከብ ባሻገር ከሚያገኘው ትርፍ የአልማ የኮርፖሬት አባል ሆኖ ለክልሉ ተጨማሪ ልማት አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅት ድጋፍና ክትትል ባለስልጠን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው ጌቴ በበኩላቸው አማራ ልማት ማህበር ከሶስት አመታት ወዲህ ብራንዱን በመቀየር እያሳየ የሚገኘው ልማታዊ እርምጃ የባለድርሻ አካላትንም ሆነ የክልሉ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱን እያጎላው ነው ብለዋል፡፡ ልማት ማህበሩ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ለምክክር ያቀረባቸው ፕሮጀክቶች የክልሉን የሰውና ፋይናንስ ሀብትን አቀናጅቶ በመጠቀም ለውጤታማ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የክልሉን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል ፈር ቀዳጅ አሰራር መሆኑን አቶ አበባው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ልማት ማህበሩ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን አዘጋጅቶ አቅም ላላቸው የኮንስትራክሽን ዘርፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የግንባታ ኮንትራት ለመስጠት ያዘጋጃቸው የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች 2 ቢሊዮን የሚጠጋ በጀት መድቦላቸዋል፡፡

Gallary


The News