አልማ እያመረተ ያለው የእጅ ንጽህና መጠበቂያ/Hand Sanitizer/ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አጋዥ እንደሆነ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ

Posted on : May: 16/20
Card image

አልማ እያመረተ ያለው የእጅ ንጽህና መጠበቂያ/Hand Sanitizer/ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አጋዥ እንደሆነ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ

አማራ ልማት ማህበር /አልማ /እያመረተ ያለውን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አጋዥ መሆኑ የተገለጸው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአልማ አመራሮች በ05/09/2012 ዓ.ም የእጅ ንጽህና መጠበቂያ የምርት ሂደቱን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈራ ወንድማገኘው አማራ ልማት ማህበር /አልማ/ በአማራ ህዝብ ተመስርቶ ለአማራ ህዝብ እየሰራ ያለ የልማት ማህበር መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ስዓትም የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንደክልል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ ማምረት መጀመሩ ለህዝብ ከቆመ ማህበር የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ አልማ በክልላችን ለሚገኙ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይጠቁ የእጅ ንጽህና መጠበቂያና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በጀት መድቦ በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ማድረስ መቻሉ ምን ያህል ለክልላችን ህዝብ ጤና መጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ማህበር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ያሉት ቢሮ ሃላፊው በአሁኑ ስዓት እያመረተ ያለው የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ በአለም ጤና ድርጅት/ WHO / መመዘኛ መሰረት የተመረተ እና 80% የአልኮል መጠን ያለው እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡ አቶ ተፈራ አክለውም የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ ምርትን በጥራትና በስፋት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለልማት ማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ፡፡ የአብክመ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሀሪ በበኩላቸው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችን ብሎም በክልላችን መከሰቱን ተከትሎ የንጽህና መጠበቂያዎች በገብያ ላይ በበቂ ሁኔታ ማግኘት አለመቻሉን በክልል ደረጃ መገምገሙን ገልጸው የአማራ ልማት ማህበር /አልማ / የችግሩን አሳሳቢነት ፈጥኖ በመገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ ማምረት መጀመሩ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ጥላሁን አክለውም አልማ የጀመረውን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ ምርት አጠናክሮ መቀጠልና የሚመረተውን ምርትም አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማድረስ በኩል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበው ልማት ማህበሩ ለሚሰራቸው ስራዎች የክልሉ መንግስት መደገፍ ያለበትን ሁሉ እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት/አመልድ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እንዳሉት አማራ ልማት ማህበር /አልማ/ በትምህርትና በጤና ተደራሽነት ዙሪያ በሰፊው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለ የልማት ማህበር መሆኑን አውስተው በአሁኑ ስዓት ደግሞ በአለም አቀፍም ሆነ በሃገራችን የተከሰተውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጥራቱን የጠበቀ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ ማምረት መጀመሩ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አለማየሁ አክለውም አልማ በዘርፉ እውቅና ያላቸውን በጎፈቃደኛ ባለሙያዎችን በመጠቀም ያመረተውን የእጅ ንጽህና መጠበቂያ /hand sanitizer/ በተለይ በገጠር ለሚገኙ አዛውንቶች ፣እናቶች ፣ወጣቶችን ህጻናት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ተደራሽ በማድረግ የኮረና ቫይረስ መከላከል ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Gallary


The News