የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት የአማራ ሕዝብ ባሕሉን፣ ወጉን፣ ጀግንነቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ቅርሱን እና ሀገር ሠሪነቱን በቋሚነት የሚዘክርበት ነው" የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ

Posted on : May: 23/21
Card image

የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት የአማራ ሕዝብ ባሕሉን፣ ወጉን፣ ጀግንነቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ቅርሱን እና ሀገር ሠሪነቱን በቋሚነት የሚዘክርበት ነው" የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ

"የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት የአማራ ሕዝብ ባሕሉን፣ ወጉን፣ ጀግንነቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ቅርሱን እና ሀገር ሠሪነቱን በቋሚነት የሚዘክርበት ነው" የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአልማ አባላትና ደጋፊዎች ለማእከሉ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በ1984 ዓ.ም ተመስርቶ በክልሉ ማኅበራዊ ልማትን በመደገፍ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አስተሳሰብ አንግቦ እየሠራ የሚገኝ የልማት ማኅበር ነው፡፡ በ2017 ዓ.ም በከፍተኛ ልማታዊ አንድነት የራስን የመልማት ችግሮች በራስ አቅም የሚፈታ ማኅበረሰብ መፍጠር የማኅበሩ ራዕይ ነው፡፡ ማኅበሩ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እና በአሶሳ የአባላት አደረጃጀት ዘርግቷል፡፡ በውጪ ሀገራትም በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በዱባይ የዲያስፖራ አደረጃጀት ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ፈንታ የተናገሩት፡፡ የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ሕብር ሠርቶ ኢትዮጵያን የሠራ፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በስፋት የሚኖርና በዓለም የተበተነ ነገር ግን ድህነት እየፈተነው ያለ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም አልማ ይህንን ፈተና ተጋፍጦ ሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጠ ያለፈ ተቋም እንደሆነም ነው ያስታወቁት፡፡ የማኅበሩን አፈጻጸም ለማሳደግ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም የሚቆይ አዲስ የተግባር ስትራቴጂያዊ የለውጥ ዕቅድ አዘጋጅቶ በትምሕርት፣ በጤና እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ነው አቶ መላኩ ያስታወቁት፡፡ ከዚህም ባሻገር በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አልማ የድርሻውን እየተወጣ ያለ ድርጅት ነው፡፡ አቶ መላኩ እንደተናገሩት ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ሐሳብ ተቀምሯል፤ ዕቅዱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደታሰበው አፈጻጸም ሊያደርሱ የሚችሉ ልምዶችም ተገኝተዋል፡፡ በተለይ ሕዝባዊ መሠረትን ለማስፋት በተሠሩ ሰፋፊ ሥራዎች ከ92 ሺህ በላይ ሁለገብ በጎ ፈቃደኞች እና ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላትን በማፍራት ባለቤትነታቸውን እንዲያረጋግጡ ተደርጓል፡፡ ከ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ ይሕ ለቀጣይ ምዕራፍ ጉልበት መሆኑን በመጥቀስም ከነባር የገቢ ማስገኛ ተቋማት ባሻገር አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ለማቋቋም ዝግጅት ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የዕሴት መልኮች የሚታዩበትና የሚዳሰሱበት ሥፍራ ያስፈልገዋል ያሉት አቶ መላኩ "የአማራ ባሕል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት የአማራ ሕዝብ ባሕሉን፣ ወጉን፣ ጀግንነቱን፣ ሀይማኖቱን፣ ቅርሱን እና ሀገር ሠሪነቱን በቋሚነት የሚዘክርበት ነው" ብለዋል፡፡ ለዚህ ባሕል ማእከል ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት 42 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቷል፡፡ ለማእከሉ ግንባታም ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ነው ያሉት፡፡ ይህ ማእከል የክልሉን ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በማስተዋወቅ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከርና የቱሪዝም መዳረሻና የመረጃ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡ ለመዲናዋ ተጨማሪ ውበት፣ የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እንደሚሆንም አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡ የማእከሉ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ የአልማ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ በፊት ከነበራቸው ተሳትፎ በበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አቶ መላኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመርኃ ግብሩም ለመስተንግዶ የተያዘው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲውል ተወስኗል፡፡ ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ በዌብሳይት www.amharaweb.com በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Gallary


The News