የመፈፀም አቅሙ እያደገና የተቋም ግንባታ ተምሳሌት እየሆነ የመጣ የልማት ማህበር ነው ሲሉ የአማራ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለፁ ፡፡
ክቡር አቶ መላኩ ፈንታ የልማት ማህበሩ 30ኛ አመት የምስረታ በዓል ዝግጅት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የህዝቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት በጥቂት በጎ-ፈቃደኞች የተቋቋመው አልማ ሶስት አስርታትን አስቆጥሮ በአሁኑ ሰዓት የሚሊዮኖች ተቋም፣ በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ የሚያሳትፍ፣ ዓለማቀፍ ረጅ ድርጅቶች ሳይቀር በዋና ፈፃሚነት በጋር ለመስራት የሚመርጡት፤ በድምር ውጤት አላማውን እያሳካ እዚህ የደረሰ ፣የመፈፀም አቅሙ እያደገና የተቋም ግንባታ ተምሳሌት እየሆነ የመጣ ተቋም ሆኗል ብለዋል፡፡ የልማት ማህበሩ መቋቋም ወሳኝና አሳማኝ ነበር ያሉት ክቡር አቶ መላኩ በቦርድ አደረጃጀት በህዝብ ተጠሪ ተቋማትና ሲቪክ አደረጃጀቶች እንዲወከል ከማድረግ ጀምሮ ኢትዮጲያዊያንና ትቀውልደ ኢትዮጲያዊያን ከጥርጣሬ ወጥተው ከማህበሩ ጋር በመቀራረብ የጋራ ፕሮጀክት እየፈፀሙበት የሚገኝ አሳታፊ የህዝብ ማህበር እንዲሆን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡ ባለፉት ሶስት የስትራቴጅ አመታት በዕቅዳችን ያህል ላለመራመድ አገራዊና ክልላዊ ሁኔታወዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም የተቋም ህልውና ከማስጠበቅ ጀምሮ በተለዋዋጭ የለውጥ ዕቅድ አላማን የማሳካት ስራ ተከናውኗል፡፡ አልማ ቀደም ሲሉ በነበሩት 21 አመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር የልማት ሀብት አንቀሳቅሶ ለክልሉ ትርጉም ያለው ስራ ያከናወነ ቢሆንም ከ2012-2014 ባሉት የለውጥ ዕቅድ ጊዜ ደግሞ ሶስት ቢሊዮን የልማት ሀብት አንቀሳቅሶ 651 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ ርክክብ ተፈፅሟል፡፡በፌታችን ሀምሌ ወርም በርካታ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አጠናቀን ለተጠቃሚው ህዝብ ለማስረከብ ዝግጅት መደረጉን ክቡር አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡ የትምህርት፣ የጤና እና የስራ ዕድል ፈጠራ ዋና የትኩረት መስኮቻችንን ሳንለቅ የህብረተሰቡ ፍላጎት ይገዛናል የሚሉት ክቡር አቶ መላኩ የክልሉ ህዝብ በሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ ችግር የተጎዳ በመሆኑ ጉዳቱ ሊያገግም በሚችልበት ደረጃ ከዘላቂ ልማታችን ጎን ለጎን አልማ የመልሶ መቋቋምና ስነ-ልቦና ግንባታ ስራዎችን በቀጣይ ስትራቴጅው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡ አልማ አላማውን ለማሳካት የልማት ሀብት የማንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ያሰመሩበት ክቡር አቶ መላኩ ከአባላትን ህዝባዊ መሰረት ከማስፋት ጎን ለጎን ዘላቂ የልማት ሀብት የማመንጨት ተግባር ለማሳካት በቴክኒዮሎጅ የተደገፈ የመፈፀም አቅም ግንባታ ስራ ወሳኝ ተደርጎ ይከናወናል ብለዋል፡፡ አልማ ፡28/10/2014 ዓ.ም ተጨማሪ መረጃዎችን ከአልማ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ በቴሌግራም https://t.me/AmharaDevtAssociation ዩቱዩብ https://www.youtube.com/user/aamharadevelopment በዌብሳይት www.ada.org.et